Thursday 16 April 2015

ማኅበረ ቅዱሳን ሳምንታዊ የኢንተርኔት ቴሌቪዥን (Online Tv) ሥርጭት ጀመረ

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ዋና ክፍል ሳምንታዊ የኢንተርኔት TV ሥርጭት መጀመሩን አስታወቀ፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን ኅትመትና ሌክትሮኒክስ ሚዲያ ዋና ክፍል ምክትል ሓላፊ አቶ አክሊሉ ለገሠ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለጹት የማኅበሩ አገልግሎት እየሰፋ በመምጣቱና ምእመናን አገልግሎቱን ለማግኘት ፍላጐታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ይህ የኢንተርኔት ቴሌቪዥን መኖር አስፈጊ ሆኗል ብለዋል፡፡ በየሳምንቱ በEBS ቴሌቭዥን ሥርጭት ለ1 ሰዓት እየቀረበ ያለው መርሐ ግብር በቂ አይደለም ወይ? ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ አቶ አክሊሉ ሲመልሱ በEBS ሥርጭቱ የማይደርስባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ ኢንተርኔት ቴሌቭዥን በሀገር ውስጥም በውጭም ያሉ ምዕመናን ኢንተርኔት እስካለ ድረስ አገልግሎቱን ማግኘት ይችላሉ፡፡ በመሆኑም የቤተ ክርስቲያንን ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዓተ እምነትና ትውፊት እንዲሁም ታሪክ በስፋት ለሕዝበ ምእመናን ለማድረሰ ሳምንታዊውን የኢንተርኔት ቴሌቪዥን አገልግሎት ጀምረናል ብለዋል፡፡ ማኅበሩ ስለ ጀመረው የኢንተርኔት ቴሌቭዥን ይዘት አቶ አክሊሉ ሲገልጹ ዛሬ ሚያዝያ 1 ቀን 2007 ዓ.ም የጀመርነው መርሐ ግብር በሳምንት ለሁለት ሰዓት ሲሆን የሦስት ወራት የሙከራ ጊዜ ያለው ዝግጅት ነው፡፡ ይዘቱም፤ ዜና፣ ማኅበራዊ ጉዳይና ትምህርተ ሃይማኖት ሲሆን ከሙከራ ጊዜው በኋላ ሌሎች ዓምዶችን በመጨመር አገልግሎቱን ለማስፋት ጥረት እናደርጋለን ብለዋል፡፡ ይህ መርሐ ግብር የወንጌል አገልግሎት ስለሆነ ከቤተ ክርስቲያን አባቶች ከምዕመናን በሙያ፣ በዕውቀትና፣ በጸሎት ድጋፍ እንፈልጋለን፡፡ በማለት አቶ አክሊሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በኢንተርኔት ቴሌቪዥኑ አማካይነት የሚተላለፉ ትምህርቶችን WWW.eotc tv.tv ላይ ማግኘት ይቻላል፡፡

No comments:

Post a Comment